በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ስራ አመራር ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ደምሴ

መስከረም 23/2016 (አዲስ ዋልታ) በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር በሚችለው ድርቅና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በሚከሰት ጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ የተጠቆመው።

በኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ስራ አመራር ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ደምሴ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎቹ ሊከሰቱ የሚችሉትን ጉዳቶች ከመቀነስ አንፃር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከክልሎች ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ነው ጠቁመዋል።

በተለይም በአየር ሁኔታ መለወጥ ምክንያት ሊኖር የሚችለው ጎርፍና ድርቅ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ሊኖር በሚችለው ዝናብ ምክንያት ሊከሰት በሚችል ጎርፍም ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከቦታው መነሳት ካለበትም እንዲነሳ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ድርቅ እንዲሁም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች ደግሞ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ከግብርና ጤና የእንስሳት ሀብትና ትምህርት ሴክተሮች ጋር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ተከትለን በቅንጅት መስራት ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል ዳይሬክተሩ።

ችግሮቹ ከተከሰቱም የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ መስራት አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ ባሮና አዋሽ ወንዞች ሞልተው የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተፈናቀሉ ቢሆንም ፈጣን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉን አንስተዋል።

ለሚከሰቱት ችግሮች የሚሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባራትን ወስዶ በአግባቡ ካለመተግበር የሚታዩ ችግሮችን እንደ ክፍተት አንስተው በቀጣይ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠር በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ጎርፍና ድርቅ የተከሰተባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች የምግብ እህልና አልሚ ምግቦች በአስቸኳይ ድጋፍ መልክ እንዲደርሱ ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር የስርጭት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።