በሕንድ የተከለከለ አልኮል የጠጡ 30 ሰዎች ሲሞቱ የተቀሩት ለአይነ ስውርነት ተዳረጉ

ታኅሣሥ 7/2015 (ዋልታ) በምስራቃዊ ህንድ ቢሃር ግዛት የተከለከለ አልኮል የጠጡ 30 ሰዎች ሰሞቱ የተቀሩት 20 ሰዎች ደግሞ ለአይነ ስውርነት መዳረጋቸው ተገለጸ፡፡

በሕንድ እንዲህ አይነት ክስተት የተለመደ ተግባር ሲሆን ሀገሪቱ የተከለከለ እና ርካሽ አልኮል በመጠጣት በርካታ ዜጎችን በየዓመቱ ታጣለች፡፡

መንግስት በነዚህ በባህላዊ መንገድ የሚመረቱ ገዳይ አልኮሎች ላይ እገዳ ቢደነግግም ስራው በጣም አትራፊ በመሆኑ እና በህገወጥ አዘዋዋሪዎች በመመራቱ የአልኮል ስርጭቱን ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሆነ ይነገራል፡፡

በነዚህ አልኮሎች ላይ ከስድስት ዓመት በፊት እገዳ ከተጣለ ወዲህ እንኳን ከአንድ ሺሕ በላይ ህንዳዊያን ይህንኑ አልኮል ጠጥተው ለሞት ተዳርገዋል፡፡

የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም ሲሉ ይተቻሉ፡፡
ዘገባው የቲአርቲ ዎርልድ ነው።