በመተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ስራ ያቋረጡ ተቋራጮች ወደ ስራ እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ

መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የልማት ፕሮጀክቶችን አቋርጠው የወጡ ተቋራጮች ወደ ስራ እንዲመለሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥሪ አቀረበ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታሁን አብዲሳ እንደገለጹት፤ በመተከል ዞን የፀጥታ ችግር ከመከሰቱ በፊት በፌዴራል፣ በክልል እና በተለያዩ የልማት አጋሮች በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረው ነበር።
የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት፣ መንገድ፣ መለስተኛ የመስኖ ልማት እና ሌሎችንም ጨምሮ በአጠቃላይ 43 የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንደነበር አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከ50 እስከ 80 በመቶ ደርሶ እንደነበረ አስታውሰው፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ተቋራጮች ስራቸውን አቋርጠው መውጣታቸውን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ባከናወነው ተግባር በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም የልማት ፕሮጀክቶችን አቋርጠው የወጡ ተቋራጮች ወደ ስራ እንዲመለሱ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በቀጣይም የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥማቸው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው፣ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው ማህበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት ለፕሮጀክቶቹ ስኬት መስራት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።