በመተከል ዞን ጉባ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሽፍቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው- የዞኑ ኮማንድ ፖስት

መጋቢት 27/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን ሰላም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ባለመቀበል በንፁሃን ላይ ግዲያ በሚፈፅሙ ሽፍቶች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል አስታወቀ።
በዞኑ ጉባ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሽፍቶች ላይ እርምጃ በመወሰድ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የግብረሃይሉ አመራሮች በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይ ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ለሶስት ዓመታት በዘለቀው የዞኑ የፀጥታ ችግር መንግስት በታጣቂዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።
በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል ኦፕሬሽን አስተባበሪ ብርጋዴል ጀኔራል ነገሪ ቶሊና ሰውን ወደ ሰላም መመለስ ትልቅ ዋጋ ስላለው ለዚሁ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል በንፁሃን ላይ ግዲያ የሚፈፅሙ ሽፈቶችን አንታገስም፤ የተጠናከረ እርምጃም ይወሰዳል ነው ያሉት።
በዚህም ጉባ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሽፍቶች ላይ እርምጃ በመወሰድ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኮማንድ ፖስቱ አመራርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በበኩላቸው የመተከል ዞን የአንድ ክልል ጉዳይ ሳይሆን እንደ አገር የሚታይ የኢትዮጵያዊያን የዐይን ብሌን የሆኑ ሀብቶችን ያቀፈ ቀጣና ነው ብለዋል።
በመሆኑም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በሚፈፅሙ የሽፍታው አባላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በመተከል ዞን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳይ ጭምር ውስብስብ ፍላጎቶች እንዳሉ በመጠቆም ችግሮቹን በጥንቃቄ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ጠላቶችም በአካባቢው ህዝቡን እርስ በርስ በማጋጨት ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንደሚሹ ገልጸው፤ ህዝቡ ይህን መረዳትና ኮማንድ ፖስቱን ማገዝ እንዳለበት ገልጸዋል።
ዜጎችን የሚገድል ሽፍታ ላይ ሰራዊቱ አሳዶ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል ።