በመተከል የተቀናጀ ግብረ ኃይል በሕዝቦች መካከል የእርቀ ሠላም ሥነ-ስርዓት እያካሄደ ነው

የካቲት 08/2013 (ዋልታ) – በመተከል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እየሰራ ያለው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በዞኑ ሕዝቦች መካከል የእርቅ ሥነ-ስርዓት ማካሄድ ጀምሯል።

እስካሁንም በዞኑ በቡለን፣ ጉባ፣ ግልገለ በለስ፣ ዳንጉር፣ ድባጤ፣ ወንበራ፣ ፓዌና ማንዱራ ወረዳዎች በ41 ቀበሌዎች ሕዝቦችን ማቀራረብ የሚያስችሉ ሕዝባዊ ኮንፍረንሶች ተካሂዷል።

በሕዝባዊ ኮንፍረንሶቹም በዋናነት የተከሰተው የጸጥታ ችግር የሕዝቡ ሳይሆን የጸረ ሰላም ሀይሎች ሴራ መሆኑ በሕዝቡ መገለጹን የተቀናጀ ግብረ ህይሉ ገልጿል።

በተመሳሳይ እስካሁን በድባጤ፣ በፓዌና መንዱራ ወረዳዎች በ18 ቀበሌዎች የሕዝቦች የእርቀ ሰላም ስነ ስርዓት ተካሄዶ ሰላም ወርዷል።

በትናትናው እለትም ከዞኑ ፓዌ እና ማንዱራ ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት የእርቅ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ በእርቅ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የመተከል ዞን ሕዝቦች አንዱ ከአንዱ ጋር ተሳስሮ የሚኖርበት መሆኑን አስታውሰዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች ጥቅምና ፍላጎታቸው እንዳይጓደል ሕዝቡ እርስ በእርስ እንዲጎዳዳ አድርገውታል ነው ያሉት።

ብርጋዴር ጄኔራሉ ከዚህ በኋላ እርስ በእርስ በመጎዳዳት ለውጥ አይመጣም ብለዋል።

ከዚህ በኋላ ያለፈውን ወደኋላ በመተው በቀጣይ የተሻለ ነገር እንዲመጣ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

መተከል ዞን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሠላም ወርዶ ሕዝቦች በጋራ ሰርተው የሚኖሩበት እንዲሆን ሁሉም ኃላፊነቱን ይወጣ ሲሉም አሳስበዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ መንግስት በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በእርቀ ሠላም ሥነ ስርዓቱ ላይ የታደሙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፣ እርቁ በአካባቢው ሠላም እንዲሰፍን ትልቅ ጥቅም እንዳለው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡