በመተከል የፀጥታና የሕግ ማስከበር ስራውን የተረከበው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ለዘላቂ ለውጥ እየሰራ ነው

የመተከል ዞንን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ስራ የተረከበው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ሃይል የዞኑን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ በዞኑ የዜጎች የጸጥታ ስጋት መቀነሱንና አንፃራዊ ሠላም መስፈኑን ገምግሟል።

የፀጥታና የሕግ ማስከበር ስራውን በአንድ ወር ጊዜ አጠናቆ ለአስተዳደሩ ለማስረከብ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቶም አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዞኑ ሙሉ በሙሉ ሠላም ሰፍኖ ዜጎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የአጎራባች የአማራና ኦሮሚያ እንዲሁም የካማሺ ዞኖች የስራ ሃላፊዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሏል።

ግብረ ሃይሉ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች ጋር ባካሄደው ምክክር ችግሩ የሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን የጥቂት አመራሮች እኩይ ተግባር እንደሆነ ማረጋገጡን ገምግሟል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዳሉት ግብረ ሃይሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት አስፈሪ የነበረውን ድባብ ወደ አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት መልሷል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህም በጉሙዝ ማኅበረሰብና በሽፍታው ቡድን መካከል ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለ በኅብረተሰቡ ዘንድ መግባባት ተደርሷል፤ ይህም አካባቢውን ወደ ዘላቂ ሠላም ለመመለስ አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።

የግብረ ሃይሉን የጸጥታና የሕግ ማስከበር ስራ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ከክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ችግር አለባቸው በተባሉ አካባቢዎች የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በቡለን፣ በድባጤ፣ በማንዱራና በወንበራ ወረዳዎች በተደረገ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሽፍታው ይንቀሳቀስባቸው የነበሩ 15 ቀበሌዎች መፅዳታቸውን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ለህይወቱ ሳይሳሳ ለሕዝቡ ሠላምና ደህንነት ዘብ የቆመ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጄኔራሉ በወታደራዊ ዘመቻ ወቅት እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት ለሽፍታው መረጃ እየሰጡ ቦታ እንዲቀየር ያደርጋሉ ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በወረዳና በቀበሌ የስራ ሃላፊዎች ግዴለሽነት አልያም በወንጀሉ ተሳታፊነት ሠላማዊ ቀበሌዎችም የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዳቆሙ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ የወረዳ የስራ ሀላፊዎች በመንግስት ተቋማት በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች አገልግሎት የማይሰጡ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ወስደው እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ የማስከበር ዘመቻ በመጀመሩ የዜጎች በሠላም የመኖር ተስፋ ለምልሟል ብለዋል።

ይህ ቀጣይነት ኖሮት ዜጎች በሠላም እንዲኖሩ፣ በመልማት ፍላጎታቸውና አቅማቸው ልክ ማደግ እንዲችሉ፣ ሕብረ ብሔራዊነታቸውን የሚቀበልና የሚተገብር አመራር እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል።