የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለማስጀመር ውይይት ማካሄዱን ገለጸ

                                                    የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለታ ተስፋዬ

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሰላምን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ከጸጥታ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ማካሄዱን ገለጸ፡፡

የዩኒቨርሰቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለታ ተስፋዬ ከዋልታ እንደምን አደርሽ ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተማሪዎች አሁን ላይ ወደ ግቢ እየተመለሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ተማሪዎች ግቢ ውስጥ ከሚደረግላቸው ጥበቃ በተጨማሪ ከግቢ ውጪ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ምክክር እና ቅድመ ዘግጅት መደረጉንም አንስተዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በደንቢዶሎ እና አካባቢው በጸረ-ሰላም ኃይሎች ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ መደፍረስ እጅግ አሳዛኝ ነበር ያሉት ዶ/ር ለታ፣ ዩኒቨርሲቲው ከግቢ ውጪ ያለው የጸጥታ መደፍረስ ስጋት ስለሚሆን ይህ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ከመንግስት ጋር ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

95 በመቶ በሚባል ደረጃ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ግቢው መመለሳቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ጥር 22/ 2013 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው የምርቃት ስነስርዓቱን ለማከናወን ማቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጸጥታ ችግር እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደታቸው ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

(በሜሮን መስፍን)