በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የምገባ መርሐግብር ሊጀመር ነው

ሚያዚያ 05/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐግብር ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ፡፡
መርሐ ግብሩን በይፋ ለማስጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈረሙም ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮና በከተማዋ የሚገኙ የሆቴል ባለቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ አራት ክፍለ ከተሞች የመመገቢያ ማዕከላት የሚገነቡ ድርጅቶች ናቸው የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ማዕከላቱ ምግብ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችም ማዕከላቱን ገንብተው ያስረክባሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተዳደሩ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ አይችሉም ብለዋል፡፡
በመሆኑም በመዲናዋ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙና ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን ጨምሮ በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ በሙከራ ደረጃ በአምስት ክፍለ ከተሞች ለመጀመር መታሰቡን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።