ከተማ አስተዳደሩ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች አስመረቀ


ጥቅምት 4/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች አስመረቀ።

በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አደነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥረር አባይ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልቃድርና ሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በከተማዋ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ከሚሰሩ ፕሮጀክቶች መካከል የመንገድ ግንባታ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህም ከተማዋን ከማስዋብና ለዜጎች ምቹ እንቅስቃሴን ከመፍጠሩ ረገድ አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ከለውጡ ማግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ከ1 ሺሕ 400 በላይ ኪሎሜትር መንገዶች ተጠናቀዋል ያሉት ከንቲባዋ 3 ሺሕ 600 የሚሆኑ ኪሎሜትር ነባር መንገዶችም ጥገና እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እናደርጋለን ባልነው መሰረት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር እያሳየን ነውም ብለዋል።

በ2015 ዓ.ም ውጤታማ የሆንንበትን ስራዎች በአዲሱ ዓመትም ለማስቀጠል ወደ ተግባር ገብተናል፤ በዚህም እንደተለመደው ህዝባችን ከጎናችን ሊቆም ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ለዜጎች ምቹ የሆነና የትራፊክ መጨናነቅን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ለመንገድ ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህ በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰራ የሚገኘው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል። ይህም ከተማዋን ከማሳደግ ባሻገር የንግድ ትስስሩም እንዲሳለጥ ጉልህ ሚናን ይጫወታልም ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በከተማዋ ተሰርተው ለምርቃት ከበቁ ፕሮጀክቶች መካከል የኮተቤ ካራ መንገድ፣ የቦሌ 22ና የአያት መሪ መንገድ፣ የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይና ሌሎችም ይገኙበታል።

በታምራት ደለሊ