በስድስት ወራት 125 ከተሞች የኤሌክትሪክ ሐይል ማግኘታቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ፍትሃዊ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በዚህም ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 161 አዳዲስ ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያኙ ለማድረግ ታቅዶ 125ቱ  የኤሌክትሪክ ሃይል አግኝተዋል።

በመልሶ ግንባታ ሥራ ደግሞ 10 አቅዶ 10 ከተሞችን ማገናኘት ተችሏልም ነው የተባለው፡፡

በአዲስና በመልሶ ግንባታ ሥራዎች 171 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ አቅዶ 135ቱን ማሳካቱንም ነው ተቋሙ የገለጸው።

ከዚህ ባለፈም ባለፉት ስድስት ወራት የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ 1 ሺህ 35 ነጥብ 15 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ ለማከናወን ተቋሙ አቅዶ 1 ሺህ 439 ነጥብ 67 ኪሎ ሜትር  በመዝርጋት ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም አሳይቷል።

በጨማሪም 749 ነጥብ 93 ኪሎ ሜትር  የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ለማከናወን አቅዶ 1 ሺህ 439 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር መዘርጋት መቻሉን ገልጿል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን 427 የትራንስፎርመር ተከላ ለማከናወን ታቅዶ 314 ያህሉ ተከናውኗልም ነው ያለው፡፡

ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ በ2013 የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 142 ሺህ 11 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙም መደረጉንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

በቀጣይም ከዋናው የኃይል ቋት የሚርቁ 25 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በሚኒ ግሪድ የሶላር ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራም እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።