በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የብርሐን ደባርቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

 

በአማራ ክልል በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የብርሐን ደባርቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።

ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው እና የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው ትምህርት ቤቱ የተመረቀው።

የቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ በሚያደረገዉ ጥረት በጽሕፈት ቤቱ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነዉን በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አስተዳደር ያስገነባዉን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬዉ እለት አስመርቋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በዉስጡ የአስተዳደር ህንጻ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ላብራቶሪ፣ የቤተ መጽሀፍ ፣ የስብሰባ አዳራሽ እና የመጸዳጃ ህንጻዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ግንባታዉ 13 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል፡፡

ትምህርት ቤቱ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአንድ ፈረቃ 1 ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም አለዉ መባሉን ከ አማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በዛሬዉ እለት ያስመረቀዉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታቸዉ ተጠናቆ ከተመረቁት ስድስተኛው ሲሆን፣ ቀሪዎቹን በቅርብ ቀን በሁሉም ክልሎች እንደሚያስመርቅም ታውቋል፡፡