በቄለም ወለጋ ዞን እየተገነባ የሚገኘውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጉብኝት ተካሄደ

ሰኔ 02/2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በቄለም ወለጋ ዞን በሰዲ ዳሌ ወረዳ ሐሮ ሳቡ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጎበኙ።
በ2012 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እና ጥራት እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል።
የግንባታ ደረጃውም 64 በመቶ ደርሷል ነው የተባለው።
ከ260 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የሚገነባው የሐሮ ሳቡ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታው ከስድስት ወራት በኋላ ከ35 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።
የከተማዋ ነዋሪ በንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንደነበረባቸው ተናግረው፣ እየተካሄደ ባለው ግንባታ መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ ፍጥነት እና ጥራት የነዋሪው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበርም ተጠቁሟል።
(በሚልኪያስ አዱኛ)