በባቡር የሚጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ ማሠራጫ ማዕከሎች እንዲደርስ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የአፈር ማዳበሪያ

ሐምሌ 18/2015 (ዋልታ) ከጅቡቲ ወደብ በባቡር ተጓጉዞ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ ማሠራጫ ማዕከሎች እንዲደርስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በባቡር ጣቢያው በየቀኑ በአማካይ እስከ 10 ሺሕ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚሠራጭ አስታውቋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ በእንዶዴ ባቡር ጣቢያ ተገኝተው በባቡር ተጓጉዞ የሚመጣው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሠራጭበትን ሂደት ተመልክተዋል።

በምልከታቸውም የባቡር ምልልስን በመጨመር የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ አቅምን ማሳደግ የተቻለ ከመሆኑም ባሻገር የጭነት ተሽከርካሪዎች ባቡር ጣቢያ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ በማድረግ ባቡር ጣቢያ ላይ የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ በአጭር ጊዜ ለማሠራጨት እየተሠራ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

ሰሞኑን የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ ሂደት የታየው የመፈፀም አቅም በቀጣይ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን ለማሳደግ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ትልቅ ትምህርት ይሆናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀናጅተው በትጋት መስራታቸው ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአፈር ማዳደሪያ ተጓጉዞ እስከሚያልቅ ድረስ በከፍተኛ ክትትል የሚሠራ መሆኑን ጠቁመው የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ሊሰሩ እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።