በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት ለመፍጠር አዲስና ጠንካራ የግብርና ፋይናንስ ሞዴል ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባኤው ንግግር ሲያድረጉ

ሐምሌ 17/2015(ዋልታ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት ለመፍጠር አዲስና ጠንካራ የግብርና ፋይናንስ ሞዴል ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጣሊያን ርዕሰ መዲና ሮም እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ በተለይም በግብርና ምርታማነት እንዲሁም በምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የብዝኃ ሕይወትን አደጋ ላይ መጣሉን ገልጸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሺኝ ችግሩን አባብሶት መቆየቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች እንዲሁም የሕዝበ ቁጥር መጨመር ችግሩን ይበልጥ ከባድ እንዳደረገው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

በዚህም በዓለም ላይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለምግብ እጦት ችግር መጋለጣቸውን አንስተው በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ቀውስ ለመከላከል አገራት በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ፍትሃዊና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት እንዲኖር አዲስና ጠንካራ የግብርና ፋይናንስ ሞዴል መፍጠር እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንዖት የሰጡት።

ይህ አዲስ የግብርና የፋይናንሰ ሞዴል ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ አገራት የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የግብርና ምርቶች የገበያ እድል እንዲያገኙና የዘርፉ እሴት ሰንሰለት እንዲጠናከርም መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል አቅም ያላቸው ወጣቶችና ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎትና የግብርና መድን ሥርዓት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

መንግሥታት የምግብ እጥረትና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮችን ለመከላከል የጠነሰሷቸውን ውጥኖች ለመደገፍ የሚያስችል ዓለማቀፍ ስርዓት መኖር አለበት ብለዋል።ት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና በምግብ እራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ መደገፍ እንዳለበትም አንስተዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግና ለማዘመን ትኩረት መስጠቷን ጠቁመው የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ማድረጓን ገልጸው በዚህም አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

ለአብነትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና በምግብ እራስን ለመቻል ከአራት ዓመታት በፊት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፈው ሐምሌ 10 በ12 ሰዓታት ውስጥ 567 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ጠቁመዋል።

የበጋ ስንዴ ልማት በአገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ የስንዴ ፍላጎት ከሟሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር በርካታ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

በከተማ ግብርናም ዜጎች ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችሉ አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌማት ትሩፋት በተለይም የእንሰሳት ሃብትን በመጠቀም የእንሰሳት ተዋጽዖ ምርትና ምርታማነት በመጨመር በምግብ እራስን የመቻል ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢዘአ ነው።