አቮካዶን ወደ ውጭ በመላክ ከ2.1 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

 

የአቮካዶ ልማት ወቅታዊ ሁኔታ፣ እምቅ አቅምና እድሎችን አስመልክቶ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) ከ2014 እስከ 2015 ዓ.ም ባለው የምርት ዘመን አቮካዶን ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር እና ኦሮሚያ ግብርና ቢሮ አስተባባሪነት የአቮካዶ ልማት ወቅታዊ ሁኔታ፣ እምቅ አቅምና እድሎችን አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአቮካዶ ልማት በግብርናው ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ኢኒሼቲቭ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በ2014 እስከ 2015 ዓ.ም ባለው የምርት ዘመን በመላው ሀገሪቱ 14 ነጥብ 5 ሚሊየን የአቮካዶ ችግኝ መተከሉም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ 20ኛዋ ከፍተኛ የአቮካዶ አምራች ሀገር መሆኗ የተጠቆመ ሲሆን አቮካዶን ከማምረት አንፃር ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላትም ተገልጿል።

አቮካዶ ከሚይዛቸው ንጥረ ነገሮችና ጤናማ ምግብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት እየተፈጠረበት የሚገኝ ፍራፍሬ መሆኑም ተጠቅሷል።

በቃልኪዳን ሐሰን