በተሳሳተ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ለመቀነስ እውነታውን የማስረዳት ሥራ በዲያስፖራው እየተከናወነ ነው – ኤጀንሲው

ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት

ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – በተሳሳተ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ለመቀነስ እውነታን የማስረዳት ሥራ በዲያስፖራው እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት፣ በውጭ ሀገር እየተደረጉ ያሉ ጫናዎችን ከመከላከል አኳያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሆኑ ሥራዎች በዲያስፖራው ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

ዲያስፖራው ከሰሞኑ አሜሪካ ያስተላለፈችውን ውሳኔ በመቃወም ሰልፍ በማድረግና በማህበራዊ ሚዲያ የተቃውሞ ዘመቻዎችን እያካሄደ መሆኑን አመልክተው፣ በየሀገሩ እየተካሄዱ ያሉ ሰልፎች ቀጣይነትም እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ዲያስፖራው የአሜሪካ እርምጃ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ጊዜ መልካም ግንኙነትን ያላከበረ መሆኑን ያስታወቁት ወይዘሮ ሰላማዊት፣ ከኢትዮጵያ በኩል ያለውን እውነታ የማስረዳት ሥራ አሁንም በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጫናዎችን መቀነስ ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው የህግ ማስከበር ሂደት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ የሚደረጉ ጫናዎችን ለመቋቋም ትክክል ባልሆኑ መረጃዎች አቋሞች ስለሚያዙ የትኞቹ ትክክለኛ መረጃዎች ናቸው? የሚለውን በመከታተል የማስተካከል ሥራ እየሰሩ እንደሆኑ ጠቁመዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።