በትግራይ ክልል ለ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ መሰራጨቱ ተገለጸ

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) –በትግራይ ክልል ለ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ መሰራጨቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ 46 ነጥብ 5 የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ 70 በመቶ የሚሆነው የእርሻ መሬት ለክረምት ወቅት ዝግጁ መሆኑ እና 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ዝግጅት መደረጉን እንዲሁም ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በተያያዘም የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሪዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ የይፋዊ የስራ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተለያዩ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የውሃ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተመራ ልዑክ በደቡብ ሱዳን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ማድረሳቸውን አንስተው፣ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ እንዲሁም በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታና በቅርቡ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ለፕሬዝዳንቱ፣ ውሃና መስኖ፣ ለኃይልና ግድቦች እንዲሁም የአከባቢና ደን ሚኒስትሮች ገለጻ አድርገዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ መግለጫው በፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን የተመለከቱም ሳምንታዊ ክንዋኔዎች መዳሰሳቸውን ከሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡