በትግራይ ክልል አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ዶክተር ሙሉ ነጋ

                                                                                       ዶክተር ሙሉ ነጋ

በትግራይ ክልል አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ካቢኔ አወቃቀርም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት የሚገፋ ቡድን ወይም ግለሰብ እንደማይኖር ማረጋገጡን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የፌዴራሉ መንግስት ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ መግለጻቸው ይታወሳል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ÷ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን በጀመረበት ወቅት የታጠቁ ግለሰቦችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የተቋረጡ ህዝባዊ አገልግሎቶችን ማስጀመርና የክልሉን ካቤኔ አዋቅሮ ወደ ስራ ማስገባት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱንም ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በፈቃዳቸው ትጥቃቸውን ለጸጥታ አካላት እያስረከቡ ይገኛሉ ያሉት ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ሸሽተው የነበሩ ሚኒሻዎችም ትጥቃቸውን አስረክበው በሰላም ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል።

በወንጀል የማይፈለጉ የመንግስት ሰራተኞችም ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውን ጠቁመው ÷የክልሉ ካቢኔም በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባቀፈ መልኩ መዋቀሩን ገልጸዋል።

የካቢኔ አወቃቀሩም ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል በአመለካከቱ ምክንያት የትኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን መገፋት እንደሌለበት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የመንግስት አገልግሎትና የፖለቲካ ፓርቲ የተለያዩ መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ዶክተር ሙሉ ጠቁመዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር አባላት በተለያዩ አካባቢዎች በተንቀሳቀሱበት ወቅት ጁንታው በመሰረተ ልማቶች ላይ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም ነው የተናገሩት።

በተለይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ መስመሮች በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳታቸው ህዝባዊ አገልግሎቶችን በሁሉም አካባቢ በፍጥነት ማስጀመር አለመቻሉን ገልጸዋል።

የፌደራል መንግስት ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከደቡብ ትግራይ ጀምሮ እስከ አዲግራት ድረስ የመብራት አገልግሎት ማስጀመር ማቻሉን ገልጸዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን በሁሉም አካባቢ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ባካሄድናቸው ውይይትች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ዶክተር ሙሉ አያይዘውም በውይይት መድረኮች ላይ ተሳታፊዎቹ ያለምንም ገደብ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

በክልሉ የአፈና ስርዓት ተንሰራፍቶ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የውውይት መድረኮቹ አዲስ የነጻነት አየርን ያለማመዱ እንደነበሩ ነው የጠቆሙት።

የትግራይ ክልልን መልሶ በማቋቋም ረገድ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ነው ዶክተር ሙሉ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር አሁን ላይ አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ በጥሩ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰብአዊ ድጋፎች በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆኑ የማጓጓዝ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስቱ ከአስቸኳይ ድጋፍ በተጨማሪ ከበጀት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ዶክተር ሙሉ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በተቋቋመበት ወቅት የፌደራሉ መንግስት ለአስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለፃቸው ይታወሳል።

በተገባው ቃል መሰረትም ለክልሉ ሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችና እገዛዎች እየተደረጉ መሆኑን ዶክተር ሙሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።