በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው

በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የኢቲዮ-ቴሌኮም ባለሞያዎች ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።

በሰሜን ሪጅን በመቐለ እና በሽሬ ያሉ ዋና ጣቢያዎች ያላቸውን አማራጭ የመገናኛ መስመሮች በሙሉ በመቋረጥ እንዲሁም የኮሜርሻል የኃይል አቅርቦት በማቋረጥ የተከሰተ ነው ተብሏል።

በተለይ በመቀሌ በሚገኘው የቴሌኮም ጣቢያ እና ከመቀሌ ከተማ ወደተለያዩ አካባቢዎች የተዘረጉ መስመሮች መቋረጣቸው ከተረጋገጠ በኋላ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል አፋጣኝ እርምጃ ስለመወሰዱም  ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ኣሳውቀዋል።

አፋጣኝ እርምጃው ባይወሰድ ኖሮ በአገር አቀፍ ደረጃም ጭምር ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር ተገልጿል።

በመቀሌ የቴሌኮም ጣቢያ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ አካላትም በደህንነት ካሜራ እይታ ውስጥ ለማየት ተችሏል፤ ጉዳዩ በፖሊስ የምርመራ ሂደት ላይ በመሆኑ ውጤቱ ሲታወቅ እንደሚገለፅም ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ባለፈው አንድ ወር ውስጥ 39.8 ቢሊየን የሳይበር ጥቃቶች ተሞክረው መክሸፋቸውን ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።

በወሩ ውስጥ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት በመሰረተ ልማቶች ላይ መሞከራቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በዚህም የተነሳ የከፋ አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ ሲደረግላቸው መቆዬቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአከባቢው የቴሌኮም አገልግሎት ለማስጀመር ሰፊ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በዚህም የተጎዱ መስመሮችን በመጠገን፣ መልሶ በማቋቋም እና አማራጭ ሃይል አቅርቦቶችን በመጠቀም በዳንሻ፣ በተርካን፣ በሁመራ፣ በሽራሮ፣ በማይፀብሪና፣ ማይካድራ፣ በኮረም በከፊል የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡

ይሁን እንጅ ሪጅኑ የቴሌኮም አገልግትን ለማስጀመር አስቸጋሪ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የሃይል አቅርቦት መቋረጥ፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች መቆራረጥ፣ በአከባቢው የሰው ኃይል ለማሰማራት አዳጋች መሆን እና ሌሎች አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ መሰረታዊ አቅርቦቶች አለመኖር መሆኑ ተገልጿል።

በዘርፉ በደረሰው ጉዳት በዝርዝር ለማየትና በዋጋ ተምኖ ለማቅረብ፤ ጥፋቱ እንዴትና በማን እንደተፈጸመ የመለየት ስራ እየተሰራ ሲሆን ሲጠናቀቅ ከፖሊስ ጋር በጋራ የሚገለጽ ይሆናልም ተብሏል።

(በሳራ ስዩም)