በፈተናዎች የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ባሻገር ገፅታ የመቀየር ስራ ይሰራል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በፈተናዎች የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ባሻገር ገፅታ የመቀየር ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሀገሪቱ ላይ የተጋረጡት የኮቪድ 19፣ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ፣ ስራ አጥነት እና ሌሎችም ችግሮች ለውጡን ባይቀለብሱም ፍጥነቱን ግን እንደቀነሱት አስረድተዋል፡፡

ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት መንግስት፣ ማህበረሰቡ እና መገናኛ ብዙሃን በቁርጠኝነት ሊዘጋጁ ያገባል ብለዋል፡፡

በፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ላይ እየተወሰደ ስላለው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና ተያያዥ ጉዳዮች ገለፃ አድርገዋል፡፡

የፅንፈኛው ቡድን አካሄድ ባለፈው ሁለት አመት ተኩል ከቀደመው ጊዜ አንፃር ተመሳሳይነትም ልዩነትም ባለው መንገድ የሚገለፅ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መመረጥ በኋላ ቡድኑ የማኩረፍ እና እራሱን የማግለሉን ነገር ማጠናከሩን ገልፀዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም መቀሌ የመሸገው ቡድን ከቃላት ዘለፋ አልፎ በግልፅ ህገ መንግስቱን የመጣስ እርምጃ ወስዷል ብለዋል፡፡

እነዚህ ግልፅ ጥሰቶች ሲፈፀሙ መንግስት ዋጋ በመክፈል በትዕግስት አልፏል ያሉት አምባሳደሩ ሀገሪቱን ሌላ ምስቅልቅል ውስጥ ላለመክተት ወዲያውኑ እርምጃ ከመወሰድ በመቆጠብ ህገ ወጥ እንቅስቃሴውን ለመታገል ተሞክሯል ብለዋል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)