በክልሉ መጭው ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ ዝግጅት ተደርጓል – የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

 

የካቲት 25/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል መጭው ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው እንደገለፁት ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጊዜውን ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይቷል።

የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ይሆን ዘንድ የተደራጀ እቅድ ተዘጋጀቶ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም እንዲሁ ገልፀዋል።

በተለይም ክልሉ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ለዚሁ የሚሆን አደረጃጀት ተፈጥሮ ስራዎች በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

“ምርጫውን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ችግሮችን በአስተማማኝ መመከት የሚያስችል ከክልል እስከ ቀበሌ የሚደርስ አደረጃጀት ተፈጥሮ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

ለሁሉም የፀጥታ መዋቅር መመሪያና ስምሪት ተሰጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ምክትል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡

(ምንጭ:- አዜአ)