በአብዬ የተሰማራው የ22ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ ግዳጁን አጠናቀቀ

የ22ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ

በአብዬ የተሰማራው የ22ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ ግዳጁን አጠናቆ ለተተኪው ለ25ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ ማስረከቡ ተገለጸ።

የ22ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አመራርና አባላት በነበራቸው የግዳጅ ቆይታ ስኬታማ ስራዎች ማከናወናቸውን የዩኒስፋ የበላይ ጠባቂና የኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ገልጸዋል።

የዩኒስፋ የበላይ ጠባቂና የኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በርከክቡ ወቅት የሰላም አስከባሪ ሻለቃው የአካባቢው ማህበረሰብ ጎሳዎች እርስ በርስ ተከባብረው እንዲኖሩና ችግሮቻቸውን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንዲፈቱ ባደረገው የማወያየትና የማደራደር ስራ በህብረተሰቡ ዘንድ አክብሮት የተቸረው ሚዛናዊና በገለልተኛ መርህ የተከናወነ እንደነበር ተናግረዋል።

የ22ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አዛዥ ኮ/ል ሰለሞን ተስፋ የተሰጣቸውን ቀጣና የዲንካና የሚስሪያ ጎሳዎች የጋራ መጠቀሚያ የሣር ግጦሽ እና የውሃ ኩሬ ያለበት በመሆኑ፣ ሁለቱም ጎሣዎች ሣይጋጩ በጋራ እንዲጠቀሙ በማድረግ፤ ችግሮች ሲከሰቱም በመፍታት ሀገሪቱ የሠጠችውን ግዳጅ አጠናቀናል ብለዋል፡፡

የ25ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አዛዥ ኮ/ል ሌንጮ ኤደኦ በበኩላቸው፣ በወሰዱት ስልጠናዎች መሠረት ሠራዊታቸው የተሠጠውን ግዳጅ ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ22ኛ ሻለቃ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም የሀገሪቱን ስም እና ዝና በማስቀጠል አሻራችንን እናስቀጥላለን ሲሉ መግለፃቸውን ከኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡