በአትክልት፣ ፍራፍሬ እና እንስሳት ሃብት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተገለጸ

በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሃብት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡

“ብራይት ፊውቸር ኢን አግሪካልቸር” የተሰኘ በግብርና ስራ ላይ ተሰማራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡

ተቋማቱ በእንስሳት ሃብት አጠቃቀምና በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ብራይት ፊውቸር ኢን አግሪካልቸር በኢትዮጵያ የ3 ዓመታት ቆይታ የሚኖረው ሲሆን፣ ለአንድ ዓመት ያህል የቴክኒክና ሙያ መምህራንን በግብርናው ዘርፍ የአቅም ማጎልበት ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡

ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር በተግባር የተደገፉ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱና ወተትና አትክልት ልማት ከስልጠና መስኮቹ የሚጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ስልጠናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ምርጥ ዘሮችን ለማብዛት እና ምጣኔ ሃብቱን ለመደገፍ የሚረዳ ነውም ተብሏል፡፡

ብራይት ፊውቸር በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ድርጅት ቢሆንም በግብርናው በሚፈጥረው የስራ ዕድል ወጣቶች ተቀጥረው የሚሰሩበትን መንገድ ይፈጠራል፡፡

በቴክኒክና ሙያ የሚማሩ ምሩቃንም ሆነ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የአቅም ማጎልበት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በግላቸው እንዲሰሩ እንደምደረግ የድርጅቱ አስተባባሪ ዶ/ር ሰሎሞን ሞገስ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚመራ ሲሆን፣ እስካሁን በተመረጡ አራት ቦታዎች የስልጠናና የተግባር ስራ እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ቢታመንበትም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ችግሮች እንዳሉም ተነግሯል፡፡

በቀጣይ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሃብት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ነው የተገለጸው፡፡
(በተስፋዬ አባተ)