በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማመጣት ጥረት እየተደረገ ነው- አምባሳደር ሽብሩ ማሞ 

አምባሳደር ሽብሩ ማሞ

ሰኔ 01/2013 (ዋልታ) – በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሟት ቢሆንም መንግስት ችግሮቹን በመፍታት ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚያስችሉ ዕቅዶችን እና ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ ሀገሪቱን በኢንዱስትሪ ለማልማት ጥረት እያደረገ መሆኑን በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለፁ፡፡

አምባሳደር ሽብሩ ከፕሬንስ ላቲና ድረገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያን ዝቅተኛ የግብርና ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ በማውጣት እ.ኤ.አ በ2030 በኢንዱስትሪ ወደ በለፀገች መካከለኛ ገቢ ወዳላት ሀገር ለመቀየር የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማውጣት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

ሀገሪቱ እየገጠሟት ያሉ ችግሮችን በመፍታትና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን በለውጥ ጎዳና ለማራመድ እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አምባሳደሩ፤ ከቀናት በኋላ በሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ከ40 ሚሊየን በላይ መራጮች፣ ከ47 በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረትና ከአውሮፓ ህብረት  በተጨማሪ አንድ መቶ አስራ አንድ የሃገር ውስጥ ታዛቢዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

ሁለገብ ከሆኑት የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ከዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያ የ86 በመቶ የውሃ ፍሰት አስተዋጽኦ ቢኖራትም እስካሁን ወንዙን አልምታ ተጠቃሚ አለመሆኗን አንስተዋል።

ግድቡ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር 60 በመቶ ለሚሆነው የገጠር ነዋሪ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማዳረስ ከማስቻሉም በላይ ለጎረቤት ሃገራትም ሃይል ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።

ሱዳን እና ግብፅ የግድቡ ግንባታ የዓባይ ወንዝ ፍሰት መጠንን ይቀንሰዋል የሚል ስጋት ቢያሰሙም ኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ መርሆዎች መሠረት በማድረግ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እየተከተለች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት አዘጋጀነት ለወራት ሲደረጉ የቆዩት በርካታ የሶስትዮሽ ድርድሮች ያለስምምነት መጠናቀቁን ድረገጹ አስታውሷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።