በኢትዮጵያ የፀጥታና ደኅንነት ኦፕሬሽን አካሄድን በተመለከተ ግምገማ እየተካሄደ ነው

የፀጥታና ደኅንነት ኦፕሬሽን

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የፀጥታና ደኅንነት ኦፕሬሽን አካሄድን በተመለከተ ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

በግምገማው ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ እንዲሁም የክልልና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በወሰነው መሰረት በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝብ ደኅንነት ስጋትን ማስወገድ፣ ለውጭ ጠላት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ያለውን የውስጥ ተጋላጭነትን መቀነስ እንዲሁም ሰላምን በማስፈን ልማትን ማረጋገጥን ታሳቢ ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የታጠቁ ኃይሎችን በመለየት መልክ ማስያዝ፣ ታጥቀውና ተደራጅተው በህገወጥ መንገድ የተሰማሩ ፅንፈኛ ቡድኖችን ወደ ህጋዊ ሥርዓት እንዲገቡ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተነግሯል።

በዚህም የፀጥታ አካላት እንዲሁም የክልል አመራሮች የፀጥታና ደኅንነትን በማረጋገጡ ሂደት የተሰሩ ሥራዎች ተገምግመው ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥ ይሆናል መባሉን ኢቢሲ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW