በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገዳማት ጽ/ቤት የ10 ሺህ ዶላር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ ገዛ

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገዳማት ጽ/ቤት በትናንትናው ዕለት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባለ አስር ሺህ (10,000) የአሜሪካን ዶላር ቦንድ ግዢ ፈጽሟል፡፡

ገዳማቱን በመወከል የቦንድ ግዢውን የፈፀሙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አባ ዕንባቆም ሲሆኑ፣ በወቅቱ ብፁዕነታቸው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባለፀጋ መሆኗን፣ ይህን ሀብት በመጠቀም መንግሥት ለሕዝቡ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን ማከናወኑም ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ለፍጻሜ የቀረበውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ቤተክርስቲያን ድጋፏን እንደምትቀጥል ገልፀዋል፡፡

የቦንድ ግዢው “ማህበረ-መነኮሳቱ ውይይት በማድረግ የወሰኑበት መሆኑን” ጠቅሰው፣ በቀጣይ በገዳማቱ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳት በግላቸው የበኩላቸውን አስተዋጽ ለማድረግ ያላቸውን ፈቃደኝነትም አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ በጨለማ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ብርሃን ይሰጥ ዘንድ፣ ሁሉም ወገናችን አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ በገዳማቱ ሥም ከተካሄደው የቦንድ ግዢ በተጨማሪ መጋቢ አባ ዘበዓማን ሳሙኤል እና አባ ገብረ ሥላሴም በግላቸው የቦንድ ግዢ ፈጽመዋል፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ  የገዳሙን አባቶች አመስግነው፣ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።