በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ተገለጸ

የካቲት 21/2013 (ዋልታ)- በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

86.8 ቢልየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 4 ሺህ 385 የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች በክልሉ ስራ መጀመራቸውን የገለፀቱ ርዕሰ መስተዳደሩ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ክልሉ ለመሳብ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዳዲስ ባለሃብቶችን መደ ፓርኩ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በመንገድ ልማት ዘርፍ በተሰራው ስራ 112 ኪሎሜት የአዲስ መንገድ ግንባታ መከናወኑን ሲገልፁ: ክልሉን ከአጎራባች ክልሎች እና ከጎሮቤት ሀገራት ጋር በመንገድ ልማት ለማስተሳሰር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍ በተሰራው ስራ 1.2 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ፕሮጄክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ሲገልፁ ከተጀመሩ ረጅም አመት ያስቆጠሩ ፕሮጄክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የጨፌው አባላትም ርዕሰ መስተዳደሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በጥልቀት ከመከረ በኋላ ሪፖርቱን በመሉ ድምፅ አፅድቆታል።

(በአሳየናቸው ክፍሌ)