የአማራ ባንክ የመስራቾች ጉባኤ ተካሄደ

 

የካቲት 21/2013 (ዋልታ)– በምስረታ ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የመስራች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

አማራ ባንክ 188 ሺህ ባለአክስዮኖች ያሉት ሲሆን 5.9 ቢሊየን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እና ቃል የተገባ7.9 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ መጠን አለው።

ይህም ማለት የተከፈለው ካፒታል መጠን 12 አዳዲስ ባንኮችን የማቋቋም አቅም ያለው ሲሆን ቃል የተገባው ካፒታል በኢትዮጵያ 16 አዳዲስ የግል ባንኮችን የማቋቋም አቅም እንዳለው ነው የተነገረው፡፡

አማራ ባንክ አሁን ያለው ካፒታል በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ ያስችለዋል ተብሏል።

የአማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጩን ሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በመዝጋት የመስራቾች ጠቅላላ ጉባኤ ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ለማካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት ስራ ላይ በዋለው አዋጅ መሰረት ጉባኤውን ማካሄድ አለመቻሉ ይታወቃል።

ብሔራዊ ባንክ መስከረም 27/2013 ዓ.ም የውክልና ገደብ ያነሳበትን መመሪያ መሰረት በማድረግ የመስራች ጉባኤውን በውክልና ለማካሄድ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ውክልና ለአደራጆች የመስጠት ሂደቱ ተከናውኗል።

በውጤቱም 88 ሺህ 645 ባለአክስዮኖች 3.8 ቢልየን የተፈረመ ካፒታል ውክልና መስጠታቸውን ተከትሎ የመስራቾች ጠቅላላ ጉባኤን ማካሄድ ተችሏል።

የመስራቾች ጉባኤ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ፣ አደረጆችና ባለአክስዮኖች ተገኝተዋል።

(በደረሰ አማረ)