በክልሉ ለበጋ ስንዴ ውጤታማነት ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም እየተሠራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ

ታኅሣሥ 6/2015 (ዋልታ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበጋ ስንዴን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተመራ ከፍተኛ አመራር በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ ዳቡስ ቀበሌ በ35 ሔክታር መሬት ላይ በክላስተር እየለማ የሚገኝ የበጋ ስንዴን ጎብኝቷል።

የባምባሲ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሊ መርቀኒ በወረዳው የሜካናይዜሽን እርሻን በመጠቀም የበጋ ስንዴን ለማልማት አየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው እስካሁን ከ200 ሔክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በወረዳው ለበጋ ስንዴ 1 ሺሕ 305 ሔክታር መሬት የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 420 ሔክታሩ መታረሱንና ለዘር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም በወረዳው በበጋ መስኖ የተያዘውን 1 ሺሕ 913 ሔክታር መሬት ለማሣካት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በክልሉ ለበጋ ስንዴ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ዘር እየተዘራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ለበጋ ስንዴን በታቀደው ልክ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የበጋ መስኖን ለማሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።