በክልሉ ለድርቅ በተጋለጡ ቀበሌዎች የምግብና ሥርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

ኅዳር 20/2015 (ዋልታ) በሶማሌ ክልል በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ እና በአየር ንብረት ተፅዕኖ ለድርቅ በተጋለጡ ቀበሌዎች የምግብና ሥርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው።

በመንግስትና በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በአርብቶ አደር አካባቢ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በጅግጅጋ ተካሂዷል።

የማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን ድጋፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ዜጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር አማካይነት ተግባዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት በአፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ባሉና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ 30 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ እና ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሐመድ ኢጌህ የኢትዮጵያ መንግስት በአርብቶ አደር አካባቢ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚቆይ የ46 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ስራው የሚተገበረው የደሃውን ኑሮ በሚለውጠው በእርሻ፣ በከብት እርባታና መሰል የስራ ዘርፎች ነው ብለዋል።