በክልሉ 5 ሺሕ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት የማሳ ልየታ መከናወኑ ተገለጸ

አሸናፊ ክንፉ

ጥር 3/2015 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 5 ሺሕ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት የማሳ ልየታ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

ከዕቅዱ ውስጥ 4 ሺሕ 951 ሄክታር መሬት መታረሱን እና ከዚህም 1 ሺሕ 886 ሄክታር በዘር መሸፈኑን ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አሸናፊ ክንፉ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን ከዕቅዱ 40 በመቶ በዘር መሸፈን እንደተቻለ ያስታወቁት ኃላፊው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የታረሱ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በዘር ለመሸፈን እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የመስኖ እርሻ መልማት በሚገባው ልክ እየለማ አለመሆኑን ጠቅሰው በሚፈለገው ደረጃ ለማምረት በመስኖ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ቲማትም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ቀይስር፣ ጎመን እንዲሁም ድንች የመሳሰሉ የአታክልትና ስራስር ሰብሎች በመስኖ ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል እንደሚገኙና ይህም በባህላዊ መስኖና እና በዘመናዊ አሰራር እንደሚለማ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ ከኅዳር ወር ጀምሮ በተከናውነው የበልግ እርሻ ወደ 28 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ያስረዱት ኃላፊው የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ግብዓቶችን ለማሟላት ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው