ህወሓት በስምምነቱ መሰረት የከባድ መሳሪያዎችን ለፌዴራል መንግስት ማስረከብ ጀመረ

ጥር 3/2015 (ዋልታ) በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ እና በኬኒያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትላንትናው ዕለት ህወሓት የመጀመሪያ ዙር ከባድ መሳሪያዎች ማስረከብ ጀመረ፡፡

ርክክቡ ከመቀሌ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጉላ ካምፕ የተከናወነ ሲሆን በርክክቡ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ታዛቢዎች ተገኝተዋል።

በቀጣናው የተሰማራው የሰራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በመንግስት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሳሪያዎች መረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

ህወሓት ለመከላከያ ሰራዊት ያስረከባቸው የመሳሪያ ዓይነቶችም ብረት ለበስ ታንኮች፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርተሮች እና ፐምፐን ያጠቃለለ መሆኑን ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ ተናግረዋል፡፡

የርክክብ ሥነ ሥርዓቱን ለመታዘብ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች የተገኙ ሲሆን ከአረካካቢዎች መካከል ብርጋዴር ጄኔራል አድዋ ልቡካን ፒተር እርምጃው የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢፌዴሪ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰላምን የማስፈን ተግባር ዓለምን የሚያስደንቅ ስለሆነ ለመላው ህዝብና ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡