ዋልታ እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ጥር 2/2015 (ዋልታ) ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት አኑረዋል።

ስምምነቱን ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሀሰን እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጫልቱ ሳኒ ተፈራርመዋል።

ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት ስምምነት በመሰረተ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሆነ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በስምምነቱ ወቅት ሚኒስቴሩ የከተማ ዘርፍ የልማት ስራዎች የሚሰሩ ተቋማትን ያቀፈ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ስምምነቱ በነዚህ ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ለማጠናከር አልፎም ለህዝብ ተደራሽ ማድረግን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ነው የገለፁት።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በዘርፉ የሚታይ ለውጥ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም ዋልታ ሚኒስቴሩ እያከናወነ የሚገኘውን ስራዎች በማድረስ ረገድ በልዩ አቀራረብ ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በሰለሞን በየነ