በክልሉ 50 ሺሕ 493 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ

አልማው ዘውዴ

ሰኔ 14/2015 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ 50 ሺሕ 493 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አልማው ዘውዴ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ለመስጠት የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከክልል እስከ ትምህርት በቶች ደረጃ ግብረኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱንና ተማሪዎች በፈተናቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የግንዛቤና ተጨማሪ ትምህርቶች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሰኔ 26 እና 27/2015 ዓ.ም ፈተናው እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊው 1 ሺሕ 80 የመንግስት፣ 15 የግል እና 8 የርቀት ትምህርት በአጠቃላይ 1 ሺሕ 103 የፈተና ጣቢዎች ፈተና እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡

በፈተና ከሚቀመጡ ተፈታኞች መካከል 25 ሺሕ 439 ወንዶች እንዲሁም 25 ሺሕ 54 ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ፈተናው በክልል ደረጃ መዘጋጀቱንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማረም ቀለም ሜዳ ከተሰኘ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት መደረጉን ገልጸው አጠቃላይ ተፈታኞች በኦንላይን መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

የፈተና ህትመት ተጠናቆ በክልሉ በሚገኙ ስድስቱም ዞኖች ተሰራጭቶ በየዞኖች ፖሊስ መምሪያ እንደደረሰና በቀጣይ በተቀመጠው መርኃግብር መሰረት ወደ ወረዳዎችና ትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጭም ኃላፊው አመላክተዋል፡፡

በፈተና ወቅት የሚያጋጥሙ ኩረጃዎችን ለማስቀረት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ኃላፊው ፈተናው ከኩረጃ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በፈታኞች፣ ሱፐርቫይዘሮችና የጣቢያ ኃላፊዎች ምደባ ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በፈተና ወቅት ችግሮች እንዳያጋጥሙ የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም የቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው