የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው – የኢትዮጵያ አየር መንገድ

መስፍን ጣሰው

ሰኔ 14/2015 (ዋልታ) የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን በጥቂት ወራት ውስጥ በማቋቋም ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ49 በመቶ ድርሻ የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ስምምነት በመውሰድ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት አየር መንገዱ በአህጉሪቷ አቪዬሽን ዘርፍ ግዙፍና ትርፋማ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በዚህም አየር መንገዱ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል የማስተዳደር ስራውን እውን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎም የተለያዩ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጀሪያ መንግስትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጀሪያ ባለሃብቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከናይጀሪያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ”የኤር ኦፕሬተር ሰርተፊኬት” ለመቀበል ሂደቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮሚቴ በማቋቋም አጠቃላይ የዝግጅት ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

በዚህም እስከ መጪው ጥቅምት ወር የናይጀሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ተቋቁሞ በረራ እንዲጀምር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

“ዝግጅቱ አሁን እያካሄድን ያለነው በመስከረም ወይም ጥቅምት ላይ አየር መንገዱ በረራ እንዲጀምር በሚያስችል ሂደት ውስጥ ነው ያለነውና በጥብቅ እየተከታተልን ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቶጎ “አስካይ አየር መንገድ” ”ከማላዊ አየር መንገድ ” እንዲሁም “ከዛምቢያ ኤር ወይስ” ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም አየር መገዱ ከኮንጎ አየር መንገድ ጋር የነበረውን ሽርክና መልሶ ለመጀመር ከኮንጎ መንግስት ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ወደ ስራ ሲገባም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአቬሽን ዘርፍ ለማስተሳሰር በሚያከናውነው ስራ ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድ ሲቋቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን 5 በመቶ የናይጄሪያ መንግስት እንዲሁም የተቀረውን 46 በመቶ ደግሞ ሦስት የናይጄሪያ ባለሃብቶች እንደሚጋሩት ተጠቁሟል።