በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዲስ አምራች ኩባንያ ተመርቆ ስራ ጀመረ

ሚያዚያ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባቲ ትሬዲንግ የተሰኘ ኩባንያ የማምረቻ ሼድ ውስጥ ማምረቻ ማሽነሪዎችን በመትከልና በመገጣጠም በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

በምረቃ መክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሀመድ አሚን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ኩባንያውን በይፋ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ለኩባንያው አመራሮችና ሰራተኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ባቲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽኑ አቅም ላላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎች የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም አሁንም አቅም ያላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ያደረገውን ያጠረ የቢሮክራሲ አሰራር እና ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን በመጠቀም ወደ ኢንቨስትመንት እንዲመጡ ጋብዘዋል።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ስራ የጀመረው ባቲ ትሬዲንግ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ጥጥን እንደ ግብዓት በመጠቀም ክር የሚያመርት ሲሆን ለምርት ሂደቱ የሚረዳ ከ1.1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የግብዓት ግዢ መፈጸሙን ከየኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኩባንያው አሁን ላይ 300 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ምርቶቹንም ሙሉ ለሙሉ ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪን በማዳን በኩል ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ይጠበቃል ተብሏል።