የጉራጌ ሕዝብ በአንድነት ውስጥ የሚገኘውን ጸጋ ከሕይወት ልምዱ የተገነዘበ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) የጉራጌ ሕዝብ በአንድነት ውስጥ የሚገኘውን ጸጋ ከሕይወት ልምዱ የተገነዘበ ሕዝብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የጉራጌ ሕዝብ ስለአንድነት እና አብሮነት አበክሮ ያስተማረና በተግባር ያሳየ አንድነት ኃይል ነው ብሎ የሚያምን መሆኑን አንስተዋል።

ስለሰላም ሳናስብ፤ ስለሰላም ሳንናገር ሰላምን ልንጎናጸፍ አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉራጌ ስለሰላም የሚያስተምር፤ በሰላም የሚኖር ሰላምን የሚያስተጋባ ሕዝብ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በየዕለቱ ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለሚያጠፉ ለአትዮጵያ ጠላቶች ጉራጌ አንድነት ኃይል ነው ብሎ ስለሚያምን ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ልንማር ይገባል ብለዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ አንድነትን ጠብቀን ለትውልድ ማሻገር እንድንችል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡