በኳታር የነገሰችው እግር ኳስ!

(ዛሬም እንደትናንት የሚታወሰው ውድድር)

በብዙ መልኩ ስኬታማ ነው ተብሎ የታመነበት የኳታሩ የአለም ዋንጫ ከተጠናቀቀ እነሆ ዛሬ ድፍን አንድ አመት ሞላው፡፡

በውድድሩ ጠቅላላ 172 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት ውድድር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ አለም ዋንጫ በፊት እ.ኤ.አ በ1998 እና 2014 የውድድር ዘመን የተቆጠሩት 171 ጎሎች ነበር ክብረወሰኑን የያዙት፡፡

የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የፈረንሳዩ የፊት መስመር ተጫዋች ክሊያን ምባፔ በ 8 ግቦች የወርቅ ጫማውን መውሰድ ሲችል ሊዮኔል ሜሲ፣ ቡርኖ ፈርናንዴዝ፣ ሀሪ ኬን፣ ኢቫን ፔሬሲችና አንቶኒ ግሪዝማን እያንዳንዳቸው 3 ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችተው በማቀበል ከላይ የተቀመጡ ተጫዋቾች ናችው፡፡

ኳታር ይህንን ውድድር ለማዘጋጀት ከ200 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገች የተገለፀ ሲሆን በሁሉም ውድድሮች 3.4 ሚሊየን ሰዎች ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎችን ተመልክተዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያው በኩል ደግሞ የኳታር አለም ዋንጫን የተመለከቱ በጠቅላላው 93.6 ሚሊየን ፖስቶች የተፖሰቱ ሲሆን እነዚህ ፖስቶች ከ260 ቢሊየን በላይ ተደራሽ መሆን እንደቻሉ የፊፋ መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ ውድድር አፍሪካ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜን መቀላቀል የቻለችበትም ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ደግሞ በመፃፍ ቀዳሚዋ ሀገር ሞሮኮ ስትሆን ፖርቹጋልን 1 ለ 0 በማሸነፍ ነበር ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል የቻለችው፡፡

የፖርቹጋሉ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአምስት ተከታታይ የአለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ግብ በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጫዋች መሆን ቻለ ሲሆን በአንፃሩ የአርጀንቲናው ልዑል ሊዮኔል ሜሲ በሁሉም የኳታሩ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ ግቦችን በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡

በሌላ በኩል በብዙዎች ዘንድ አይረሴ ተደርጎ የሚታወሰው የአርጀንቲና እና የፈረንሳይ የፍፃሜ ጨዋታን በመላው አለም ወደ 1.5 ቢሊየን የሚጠጋ ሰው ተከታትሎታል፡፡

ይህን ጨዋታ አይረሴ ካደረጉት አጋጣሚዎች መካከል በጨዋታው መገባደጃ ላይ የፈረንሳዩ ኮሎ ሙዋኒ ያልተጠቀማት ግልፅ የግብ ዕድል ይጠቀሳል፡፡ አጋጣሚው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎችን ያስቆጨ በአንፃሩ የአርጀንቲና ደጋፊዎችን ያስደነገጠ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በመጨረሻም የ2022ቱን የአለም ዋንጫ በሊዮኔል ሜሲ የሚመራው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በፍፁም ቅጣት አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡

የሆነው ሆኖ ይህ ብዙ ታሪክና ትውስታ ያለው የኳታሩ የአለም ዋንጫ እነሆ ዛሬ ከተጠናቀቀ ድፍን አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡

በሳሙኤል ሙሉጌታ