ጤናና የህይወት ዘይቤ – የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ

 

ጤናችን አኗኗራችንን ይመስላል፡፡ የምመገባቸው ምግቦች ዓይነት መጠንና ስብጥር የምንወዳጃቸው ሰዎች ባህርይ የስራ ባህርያችን ስለንፅህና ወዘተ በጤናችን ላይ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡

“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለው ፈሊጣዊ አነጋገር የቅድመ መከላከልን ጠቀሜታ እና አስፈላጊነት አፅኖት ይሰጣል፡፡ በህመም ወቅት የሚያጋጥመንን ስቃይ አለመመቸት እንዲሁም በህክምና ወቅት የሚኖርን የመድኃኒት አለመመቸትም ይሁን ከዚያ ወጭ ድካም በህመም ምክንያት መማቀቅን (መሰቃየትን) ይጠቁማል፡፡

“አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለው የፈሊጣዊ ንግግሩ አካል ደግሞ እነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ህመምና ስቃይ በቀላሉ ቀድሞ ጥንቃቄ በመውሰድ እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚቻል ያመላክታል፡፡

የጤና የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች ደግሞ ለመተግበር ቀላል ወጭው ለህክምና ከምናወጣው በአንጻራነት ያነሰ ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

በመሆኑም በኑሮ ዘያችን ልንከተላቸው የሚገቡ የጤና ቅድመ መከላከል እርምጃዎች ከሚባሉት ውስጥ ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ለማየት እንሞክር፡፡

ሀ. የተመጣጠነ ምግብ መመገብ

ለሰውነትታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ምግቦችን መመገብ ለጤናችን እጅግ መሰረታዊ ነገር ነው። በመሆኑም ጥራጥሬ አትክልት የወተት ውጤቶችን ቀይ ስጋና ፍራፍሬዎችን በበቂ መጠንና ዓይነት በመመገብ ጤናማ ያልሆኑና ስብና ጮማነት ያላቸው ምግቦች ጨው የበዛበትና ጣፋጭ ምግቦችን ከመመገብ መታቀብ ይመከራል።

ለ. ዘወትር የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ

በየቀኑ ከ15-30 ደቂቃ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤንነት ይመከራል።አካላዊ እንቅስቃሴዎቹ ሩጫ ዋና እርምጃና የነዚህ ስብጥር ወዘተ ሊሆን ይችላል። በስፖርት መስሪያ ቤቶች መሄድ ሳያስፈልግ በአካባቢያችን ባሉ አነስተኛ ስፍራዎች እንቅስቃሴ ማድረግ ቅርብ ለሆኑ ቦታዎች በተሸከርካሪ ከመጓዝ እንዲሁም አሳንሰር ከመጠቀም ወዘተ በእግር መጓዝ ይመከራል፡፡

ሐ. ውሃ በብዛት መጠጣት

ውሃ በሰውነታችን የምግብ ልመትንና መመጠጥን (absorption) የደም ዝውውርን እንዲሁም የሰውነታችንን ሙቀት መጠን ለማስተካከል ይጠቅማል።

በየቀኑ ውሃ በብዛት መጠጣት ሰውነታችን ስራውን በአግባቡ እንዲከውንና የማይፈለጉ ነገሮችን ከሰውነታችን በላብና በሽንት መልክ ለማስወገድ ይጠቅመናል።

መ. በየተወሰነ ጊዜ ሙሉ የጤና ምርመራ ማድረግ

በየተወሰነ ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ በሽታን ቀድሞ ለማወቅና ለመከላከል እንዲሁም የተከሰተን ህመም ሳይብስብን ፈጥኖ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል።

ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ አጠቃላይ የጤና ምርመራ የማድረግ ልምድ እንዲኖረን ይመከራል፡፡

ሠ. የአእምሮ ጤናን መጠበቅ

የአእምሮ ጤና የጤናችን ሁሉ መሰረት ነው፡፡ የአእምሮ ጤንነት ችግር ያለበት ሰው ለሌሎች የጤና ችግሮች ሊያስብም ሆነ ሊጠነቀቅ አይችልም፡፡

ጭንቀትን ለመቀነስ የሚያግዙ እንደ ጫና መቀነሻ መላዎች (stress management)፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ተግባራ (hobbies) ወዘተ የአእምሮ ጤናችን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ናቸው፡፡

ማህበራዊ ግንኙነታችን ከመልካምና አዎንታዊ ባህርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ሲሆን ስሜታችንን በመጠበቅና ድጋፍ በማድረግ ያግዙናል።

ረ. አልኮልና ሲጃራ አለመጠቀም

ትምባሆ ከማጨስ መቆጠብና አልኮል መከመጠጣት መቆጠብ ካልተቻለ መጠኑን መመጠን ከዘርፈ ብዙ የጤና ቀውሶች ልንጠበቅ እንችላለን።

ለመዝናኛ ተብለው ከሚወሰዱ ሌሎች አደገኛ እፆች ፈፅሞ መራቅ ያስፈልጋል።

ሰ. የአደጋ መከላከያዎችን በአግባቡ መጠቀም

በዓለም ላይ የአደጋ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ባለመጠቀም እና/ወይም በአግባቡ ባለመተግበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።

በመሆኑም መኪና አሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶ ማድረግ በግንባታ ቦታዎች የጭንቅላት መከላከያና ሌሎች የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ በመውሰድ ከአደጋና ጉዳት ራሳችንን መጠበቅ ይገባል።

ሸ. የግል ንፅህናን መጠበቅ

መሰረታዊ የሚባሉ የግልና የአካባቢ ንፅህና ሁኔታዎች ጤናችንን በከፍተኛ ደረጃ በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ የመለወጥ አቅም አላቸው። የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት ለልዩ ልዩ በሽታዎች ያጋልጣል።

የምንመገበው ምግብ የመመገቢያ ዕቃዎች ምግቡ የሚዘጋጅበት ቦታ የምንመገብበት እጃችን የንፅህና ጉድለት ካለበት ለበሽታ መጋለጣችን አይቀሬ በመሆኑ ለንፅህና ትኩረት መስጠት ይገባናል።

ቀ. በቂ ረፍት ማድረግ

በቂ እንቅልፍ አለማግኘትና የስራ ጫና ለጤና መቃወስ ይዳርጋሉ፡፡ የስራችንንም ውጤታማነትና ጥራቱን ይቀንስብናል።

በመሆኑም ሰውነታችን ከድካም መልሶ እንዲያገግምና እንዲታደስ በቂ እንቅልፍና እረፍት ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ሳንታመም እንታከም ጤናማ የአኗኗር ዘዬ ምርጫችን ለረጅምና ጤናማ ህይወት እንዲሁም ለውጤታማነት እና የሰመረ ማህበራዊ መስተጋብር እጅግ ቁልፍ ሚና አለውና የዕለት ተዕለት ተግባራችን እናድርግ፡፡ ጤና ይስጥልን!!

 

በቴዎድሮስ ሳህለ