በዞኑ ለምርት ዘመኑ ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው

 

መጋቢት 25/2016 (አዲስ ዋልታ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ለ2016/2017 የምርት ዘመን ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዚህ የምርት ዘመን ካለፈው ዓመት በተሻለ ማዳበሪያ ቀድሞ በመቅረቡ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ስራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ ኃይለ ኢየሱስ ዳምጤ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ የቀጣይ መኸር ወቅት ሰብል ልማት ስራውን ወቅቱን ጠብቆ እንዲያከናውን ማዳበሪያ ቀርቧል።

በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ግዥ ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው እስካሁን በተደረገ ጥረት ግማሽ ሚሊዮን ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መጓጓዙና ከዚህም ውስጥም 148 ሺሕ ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።

ማዳበሪያው በጎዛምን፣ ሞጣ እና ጊወን የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማኅበራት ዩኒየን እንዲሁም በመሠረታዊ ኅብረት ስራ ማኅበራት በማራገፍ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቅሰው ቀሪውን ማዳበሪያም በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ባለው ጊዜ ሙሉቀን እንዳሉት ለመጪው የመኸር ወቅት ሰብል ልማት የሚውል ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ መውሰዳቸውንና ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ለመጠቀም አቅደዋል።

በዘንድሮ ዓመት ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ማዳበሪያው ቀድሞ መግባቱ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ስራ ለማከናወን ያስችላል ያሉት ደግሞ በአነደድ ወረዳ የወቢ እነችፎ ቀበሌ አርሶ አደር ማስረሻ ደግሰው ናቸው።

ባለፈው ዓመት ማዳበሪያ እጥረት በማጋጠሙና ዘግይቶ መግባቱ በግብርና ስራው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ ግን ቀድሞ በመግባቱ ችግሩ እንደተቃለለ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።