በዴልታ ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) በአዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ዴልታ ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር የብሄራዊ የኮቪድ-19 ምላሽ ግብርኃይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ የኮቪድ-19 ምላሽ ግብርኃይል ዋና አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ማሴቦ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በዴልታ ቫይረስ ዝርያ እየተያዙ ወደ ፅኑ ህሙማን መከታተያና ማቆያ ክፍል የሚገቡና በየዕለቱ ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ ያሉ ታማሚዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ መጥቷል።

በሀገሪቱ በአሁን ሰዓት እየሞቱ ያሉት ፣ በወረርሽኙ ተይዘው ወደ ፅኑ ህሙማን መከታተያና ማቆያ ክፍል የሚገቡ ሰዎች መሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ክትባቱን ያልወሰዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ወደ ፅኑ ህሙማን መከታተያና ማቆያ የሚገቡ፣ በየቀኑ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር መበራከት ዋነኛው ምክንያት አደገኛው ዴልታ የኮቪድ-19 ዝርያ በሀገሪቱ መግባቱ ተከትሎ ነው።

ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ ገብቶ በርካታ ጉዳት እያስከተለ ቢሆንም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎች አናሳ ናቸው ተብሏል።

በየቦታው መሰባሰቦችና የመከላከያ መንገዶችን አለመተግበርም በስፋት እንደሚስተዋልም ባለሙያው መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።