በድህረ ምርጫ ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመታደግ የቦርዱ ፍትሀዊና ገለልተኛ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ተገለፀ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – በድህረ ምርጫ ወቅት የሚከሰቱ ሁከቶችና ብጥብጦችን ለመታደግ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍትሃዊና ገለልተኛ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ተገለፀ።

ከምርጫ በኃላ የሚከሰቱ አለመግባባቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ከምርጫ በኃላ ያሉ ስጋቶችና ዕድሎች ምንድነው? የሚል ሀሳብ ለውይይት የቀረበ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ ምርጫ 97 የተከሰተውን ምንድነው? 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከምርጫ 97 ምን መማር አለበት የሚሉ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።

ከምርጫ በኃላ ለሚነሱ ብጥብጦች ለኳሽ እና አስቀጣይ ምክንያቶች ተብለው ተቀምጠዋል። ለኳሽ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተቀመጡት ጉዳዮች መካከል የምርጫ መጭበርበር፣ የድምፅ ቆጠራ ቀን እንዲሁም የውጤት መዘግየት በድህረ ምርጫ ወቅት ለሚነሱ ብጥብጦች ምክንያት መሆናቸው ተጠቁመዋል።

ከምርጫ በኃላ የአሸናፊ ወይንም የተሸናፊ ደጋፊዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድጋፋቸውንም ሆነ ነቀፌታቸውን በሚገልጹበት ወቅት የሰላም አስከባሪ አካላት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ተነስቷል።

ድህረ ምርጫ ሰላም እንዲሆን ከገዥው ፖርቲ፣ ከፀጥታ አስከባሪዎች፣ ከተፎካካሪ ፖርቲዎች  እንዲሁም ከሲቪክ ማህበራት ምን ይጠበቃል የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል።

(በዙፋን አምባቸው)