በገቢ አሰባሰብ የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር በ2022 ሀገራዊ ወጪን በሃገራዊ ገቢ መሸፈን የሚለውን ራእይ እውን ለማድረግ የአሰራር ወጥነትን ለማምጣት የሚያግዝ ከክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ለተወጣጡ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ስልጠናው በተለይም ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር በመገንባት የገቢ አሰባበሰቡን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የገቢ አሰራር ስርአት በመላ ሀገሪቱ ለመዘርጋት ዓላማ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይ 10 አመታት ለማሳካት ያቀደውን እቅድ ከግብ ለማድረስ፣ የገቢ ስርአቱን በማዘመንና ፈጣን የሆነ አገልግሎት ለተገልጋዩ በመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት መሰብሰብ እንዲቻል ተሳታፊዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው

ከአስር አመት በላይ በስራ ላይ ሲተገበር የቆየው የሲግታክስ የአሰራር ስርአት ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች ሲከናወን መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ እንቅፋት የሆኑ የህግ ማእቀፎችንና መዋቅሮችን ለማሻሻል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የታክስ ትራንስፎርሜሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አዲስ ታምሬ በበኩላቸው፣ የፌዴራል እና የክልል ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት የተጣጣመ የአሰራር ስርዓት በማምጣት የሚጠበቀውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ የሚደግፍ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የክልሎችና የፌዴራል ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት የተቀናጀና የተናበበ የአሰራር ስርአት መኖር የተገልጋዩን የአገልግሎት እርካታ ከማሳደጉ በተጨማሪ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት እንዲሰበሰብ ከማድረግ አኳያ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ተሰታፊዎቹ ማብራራታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡