በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረሙ

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና “ኢንተርኔት ሶሳይቲ” በገጠር የበይነ-መረብ ግንኙነትን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የተጀመረውን ስራ የሚደግፍ፣ በገጠር ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነትን (ኢንተርኔትን) ለማዳረስ፣ የበይነ መረብ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋትና የበይነ መረብ አስተዳደርን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒኤችዲ) እና የ”ኢንተርኔት ሶሳይቲ” የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ፒኤችዲ) ፈርመውታል።

ዶ/ር አህመዲን በዚሁ ወቅት አካታች ብልፅግናን ማረጋግጥን ግቡ አድርጎ የተዘጋጀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እውን እንዲሆን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ማህበራት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ስትራቴጂው መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የዲጂታል መተግበሪያዎችን ማልማት እና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር የሚሉትን ስለማካተቱም አብራርተዋል።

ስምምነቱ ይህንን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።

ዶ/ር ዳዊት በበኩላቸው ስምምነቱ የገጠር የበይነ መረብ ግንኙነትን በማሳደግ በገጠር ያለ ሁሉም ማህበረሰብ በዲጂታል ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ የዲጂታል የኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራን ለመደግፍ ቁርጠኛ መሆኑም አረጋግጠዋል።

ስምምነቱ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቅድሚያ የተሰጣቸውን የግብርና፣ የማምረቻ፣ የአገልግሎትና የቱሪዝም ዘርፍን ለመደገፍ ያግዛልም መባሉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።