“ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ”  ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ነው

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – በዓለም በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩት መስኮች ውስጥ አንዱ የሆነው “ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ” ላይ ያተኮረ ስልጠና በኢትዮጵያ መስጠት ተጀመረ።

ስልጠናው የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የዳታ ሳይንስ ቡድን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

ከፍተኛ የዳታ ሳይንስና ምልከታ መስክ በዓለም በቅርብ ጊዜ ከተጀመሩት መስኮች አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ለጀመረቻቸው የተለያዩ የትኩረት መስኮች ውጤት የሚያግዝ መሆኑ ታምኖበት የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

ስልጠናው ሀገሪቱ ለምታደርገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትና በተለይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ስኬት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አቅም በመገንባት ረገድ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ባዩ (ዶ/ር) በስልጠናው መክፈቻ ላይ “ስልጠናው ኢትዮጵያ በዘርፉ የሰለጠኑ ሰዎች እንዲኖራትና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት በቀለ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ስልጠና ሲሰጥ የመጀመሪያው እንደሆነና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በበይነ መረብ የሚሰጠው ስልጠና ለ10 ተከታታይ ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስት መሥሪያ ቤቶች፣ በዘርፉ ከተሰማሩ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የተውጣጡና መመዘኛውን ያለፉ 55 ሠልጣኞች እንደሚታሳተፉ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።