በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ከመተከል ዞን የሀገር ሽማግሌዎች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ

መተከል ዞን የሀገር ሽማግሌዎች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ከመተከል ዞን የሀገር ሽማግሌዎች እና የኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡

የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ሌ/ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ በከሰረው ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የማዳከም ተልዕኮ፣ እኩይ ቡድኖች በማደራጀት በመተከል ዞን በጅምላ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውሰው፣ የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማ የግድቡን ግንባታ ማስተጓጎልና ከተቻለም ማስቆም ነው ብለዋል።

የግድቡን ግንባታ ማስተጓጎል ምኞት እንጂ በተግባር የሚሞከር አለመሆኑን ሌ/ጀነራል አስራት ዴኔሮ ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፣ የሕወሓት ቡድን ብሔርን ከብሔር በማጋጨት ኢትዮጵያ ውስጥ የማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመክፈት ምኞት ቢኖረውም ምኞቱ ሕልም ሆኖበት ተቀብሯል ብለዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች እና የኅብረተሰቡ ተወካዮች በሰጡት አስተያየታቸው፣ መቼም ቢሆን ሕዝብ ለሕዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም፤ እኛም ለረጅም ዓመታት አብረን የኖርን ሕዝቦች ነን፤  የእሱ ተላላኪዎች የሆኑትን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።