በፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና በጅግጅጋ እየተሰጠ ነው

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – የሰላም ሚኒስቴር በፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ ለሶማሌ ክልል አመራሮች በጅግጅጋ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ሚኒስቴሩ ከመጋቢት 18 እስከ መጋቢት 20 2013 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መሆኑ ተመላክቷል።

በስልጠናው በክልሉ ከሚገኙ 11 ዞኖች፣ 93 ወረዳዎችና 6 የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።

የስልጠናውን የሰጡት የሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝምና የመንግስታት ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፀጋብርሀን ታደሰ፣ በኢትዮጵያ በየአካባቢው በፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ላይ የሚስተዋሉ የተለያዩ ብዥታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ስልጠናው  እነዚህን የአመለካከትና የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማሻሻል የተዘጋጀ መሆኑንም አንስተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በቀጣይ ወደ የመጡበት አካባቢ ሲመለሱ በተዘጋጁት የስልጠና ማኑዋሎች በመታገዝ ማህበረሰቡን የማሰልጠንና የማወያየት ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።