በ85 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ

ሚያዚያ 1/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በኩታበር ወረዳ በ85 ሚሊየን ብር የተገነባው እናት የዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ፡፡

ፋብሪካው አሁን ላይ በቀን ከ500 ኩንታል በላይ ሲያመርት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 1 ሺህ ኩንታል የቦቆሎ ዱቄት የሚያመርት መሆኑን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ይማም አሊ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ፋብሪካው 150 ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር  የቻለ ሲሆን  ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ300 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የተገነባው ፋብሪካ በቆሎን በመፍጨት እና እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ወሎ ዞን ም/አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ ይህ ዘመናዊ ሆነ ፋብሪካ በቀን እስከ 1ሽህ ኩንታል የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰው ከስራ እድል ፈጠራ ያለው አስተዋፅኦም ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡