ግራጫው ሚዲያ

ግራጫው ሚዲያ
/ባለፉት አምስት ዓመታት/

በሳሙኤል ሙሉጌታ

መጋቢት 21/2015 (ዋልታ) ሲያሻው በውሸትና ጥቅም ሰክሮ ከቱቦ የሚወድቀው፤ ሲለው ደግሞ እንደ ሶቅራጠስ በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ እንኳ እውነትን ከመስበክ የማይቦዝነው ግራጫው የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሲቃኝ!

በሀገር ገፅታ ግንባታ ውስጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የሚችል መሃንዲስ ነው፡፡ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆኖ ለእውነት ታግሎ ነጻ የሚያወጣ ታጋይ ነው። በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደርና ቀይ መስመር ያለው ብርቱ ሰራዊትን የያዘ ዘብ ነው፡፡ አዲስ ነገርን በጆሮ አቀባይ፤ በአራቱም ማዕዘናት የተተከለ አራት አይን ያለው መረጃ ተቀባይ፤ ስሜታዊነትና አድሏዊነት በተሰኙ ባህር ውስጥ ያልረጠበ፤ የህዝብን ዕምባ አድራቂ፤ የደስታ አብሳሪና ተመስጋኝ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ወይም ሚዲያ!

ደግሞም በዕንዝላልነት ብዙ ጥፋቶችን ሊያስከትል የሚችል ተወቃሽ ይሆናል፡፡ በሩዋንዳ የሁቱና ቱትሲን የ100 ቀናት ዘግናኝ ግጭት እንዲነሳ ያደረገው አንድ ኃላፊነት የጎደለው RTLM የተሰኘ የሬዲዮ ጣቢያ ነበር፡፡ የበርካታ ሺዎች ንፁሐን ነፍስ እንደ ቅጠል እንዲረግፍ ያነሳሳው ይህ ጣቢያ ዘመን ይቅር በማይለው ጥፋት ውስጥ ዘላለም በሀገሩ ልጆች ሲብጠለጠል ይኖራል፡፡ የጣቢያው ባለቤትም ራሱን ደብቆ ከነበረበት ከፈረንሳይ ሀገር ተይዞ ለፍርድ መቅረቡ ይታወቃል፡፡

ብቻ በጥቅሉ ሀገር መገንባትም ሆነ ሀገር ማፍረስ የሚችል ታላቅ ጉልበት ያለውና በሚወስደው ኃላፊነትም እንደ አራተኛ መንግስት የሚቆጠር የሙያ ዘርፍ ነው፡፡
ታዲያ በሀገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በሚታይ መልኩ ዘርፉ መነቃቃቱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ አላማውን ዲሞክራሲ አድርጎ ወደ ስልጣን የመጣው የለውጡ መንግስት የሚዲያ ነፃነት ጣዕምን ሁሉም ይቀምሰው ዘንድ በብፌ አቅርቧል፡፡

በዚህም ሂደት ውስጥ የታሸጉ ቢሮዎች ተከፍተዋል፤ የደረቁ ብዕሮች ዳግም ቀለማቸውን ተፍተዋል፤ የተኛው ተቀስቅሷል፤ እሳቱን ሳይፈራ በአቋሙ የፀናውና የተጋፈጠው ይበልጥ ደረቱን ነፍቷል፤ በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች እጃቸው ከካቴና ተላቆ ብዕር ጨብጧል፤ ሀገሬን በማለታቸው ብቻ ከሀገራቸው የተሰደዱ ብዙ የሚዲያ ሰዎች ለሀገራቸው በቅተዋል፤ ሁለተኛ የሳተላይት ሳህን ማስገጠም ቀርቶ ሁሉ በአንድ እንዲሰበሰብ ተደርጓል፤ ሀሳብን በነፃነት መናገር መብት ሆኗል…. ወዘተ፡፡ ምን አልባትም በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ በዚህ ደረጃ እንዲህ ነፃነት የነገሰበት አጋጣሚ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

እነዚህ ወቅቶችም ለዘርፉ የብርሃን ፀዳልን የፈነጠቁ መልካም ጊዜያት ሆነው ቆይተዋል፡፡ ሁሉም እውነትና ፍትሕ ያለውን ይሰራ ዘንድ ሜዳው ክፍት ሆኖለታል።
የመንግስትም ሆኑ የግል ሚዲያዎች የህዝብን ጥያቄ አንግበው የብዙ መስሪያ ቤቶችን በር አንኳኩተዋል፡፡ ብርቱ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፡፡ ከመንግስት ወደ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የህዝብን ይዘው ወደ መንግስት ተራምደዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በዘጋቢ ፊልሞቻቸው በኩል በስልጣን ስም ሲፈፀሙ የነበሩ ግፍና ድብደባዎችን አጋልጠዋል፡፡ የጨለማው ዘመን መገፈፉን አብስረዋል፡፡

በለውጡ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ የሚዲያ ታጋዮች በነፃነት ይሰሩ ዘንድ ተፈቅዶ በሀገራቸው አፈር ላይ ቢሯቸውን ከፍተዋል፡፡ መፅሄቶች የሳለ ብዕራቸውን ዳግም መክተብ ጀምረው ብዙኃኑን አንባቢ አድርገዋል።
በማህበራዊ ሚዲያውም ቢሆን የዜጋ ጋዜጠኝነት (citizen journalism) በስፋት ተተግብሯል፡፡ ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጪ ያለው ማህበረሰብ መረጃዎችን የማጋራት መብት በማግኘቱ ፍሰቱን፣ መጠኑንና ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡ ጥሩ የሚሰራውን አወዳሽ መስመር የሳተውን ወቃሽ የመሆን መብት አግኝቷል። የሌላውን ስብዕና በማይነካ ግዴታቸው ውስጥ በነፃነት የመናገር መብታቸውን በአግባቡ ተጠቅመዋል።

ደሞም ሁሉም ልዩነቱን ይዞ ቀይ መስመራቸው የሆነችው ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትወድቅበት ሰዓት አለሁልሽ ብለው ብዕራቸውን እንደ ጦር ብራናቸውን እንደ ጋሻ ታጥቀው ከውጊያው በአንድነት ከተዋል፡፡ በሰሜኑ የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የተነሳውን የመረጃ ጦርነት ከጎልያዶቹ የምዕራባዊያን ሚዲያ ጋር በመጋፈጥ ጠጠራቸውን ወርውረዋል፡፡ ዳግማዊውን አድዋ በሚዲያ ተራራ ላይ ፈፅመዋል፡፡

የ #nomore እንቅስቃሴን ከትንሽ እስከ ትልቁ ከጫፍ ጫፍ ተቀላቅሏል፡፡ ሽንፈት የማታውቀው ኢትዮጵያ ከምዕራባዊያን የወቅቱ ዘገባ ባሻገር ሌላ እውነት እንዳላት አስመስክራለች። ከግል ሚዲያ እስከ መንግስት፤ ከፌስቡክ እስከ ትዊተር፤ ከቴሌቭዥን እስከ ጋዜጣ ሁሉም ትኩረቱን ለሀገር በማድረግ ውሸቱን አጋልጠዋል።

ከሀገር ቀጥሎ ሌላኛው ህልውናችን በሆነው በአባይ ግድብ ሲመጣም በአንድነት እንደ ፏፏቴው ፈሷል። ብዙ ጀግኖች በየዓለም አቀፉ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ሙግታቸውን አሸንፈዋል። በኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባርና ወኔ ህዝቡ ለመንግስት ድጋፉን፤ ለግድቡ ደግሞ አይደራደሬነቱን አሳይቷል። ከመንግስት የሚወጡ መግለጫዎች ህዝቡን አበርትቷል። አንዱ ለአንዱ ድጋፍ እየሆነ ስራዎች ቀጥለዋል። ይኸው አሁን ለአራተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ዝግጅት ተጀምሯል፡፡

ብቻ ሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለዚህ ታላቅ ሙያ በሰጠችው ክብር ክብሯን አስጠብቃለች፡፡ ድሏን አሳውጃለች፡፡ ብዙ አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች አፍርታለች፡፡ የተስፋ ብርሃኖች በትዕይንተ መስኮቶች (ቴሌቭዥን) በኩል ተፈንጥቀዋል፡፡ የሬዲዮ ድምፆች ስለ ፍትሕ ጮኸዋል፡፡ ፊደላት እውነትን አስሰዋል……..

ዳሩ ግን ይህን የከፍታ ጉዞ የሚያስተጓጉሉ እንቅፋቶችም አብረው ተዘርተዋል፡፡ ሁሉም ነፃነት ራሱን የቻለ ኃላፊነት አለው፡፡ ታዲያ ይህን ኃላፊነት በመርሳት ወይ በመተው መብቱን መጠቀም ያልቻለ ግለሰብና ጣቢያ በታየው ተስፋና ብርሃን ላይ ጥላሸት ቀብቷል፡፡ ሀገርን ማዋረድ፤ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት፤ የሌሎችን ክብር መንካት፤ ያልተፃፈ ማንበብ፤ ሲደረግ ያልታየውን ዐይኔን ግንባር ያድርገው እያሉ መዘገብ፤ በኋላም ተጠያቂነት ሲመጣ መብትና የሚዲያ ነፃነት በሚል ዋሻ ውስጥ መደበቅን ፋሽን ያደረጉ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ከዚሁ ከአምስት ዓመታቱ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ተሰጥቶ የነበረውን ወሰን አልባ ነፃነት እየገደበ የሚገኝ ሲሆን የሚዲያው ጉዞ ወደነበረው ቁልቁለት እንዳይወርድ ያሰጋል፡፡

ብቻ በጥቅሉ በተስፋው ተደስተን በደማቅ ብርሃን ስንወክለው የሚደበዝዝብን፤ ጨለመ ብለን ሀዘን ልንቀመጥ ስንል ዳግም የሚነጣውና የሚፈካው ግራጫው የኢትዮጵያ ሚዲያ በሀገሪቱ የከፍታ ጉዞ ላይ ማርሽ ቀያሪ ነውና ከፍተኛ ትኩረት ሊያሻው ይገባል፡፡ በመሆኑም ከመብረር ወደ መሮጥ፤ ከሩጫ ወደ እርምጃ፤ ከእርምጃ ወደ መዳኽ እንዳያዘግም በኋላም ወደ ነበረበት የዝቅታ ደረጃ እንዳይገኝ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡