ባለፉት ሁለት ዓመታት በሴት አርብቶ አደሮች ላይ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ

ሴት አርብቶ አደሮቹ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸው ለማስቻል በተወሰዱ እርምጃዎች የተሻለ አቅም መፍጠር መቻላቸው ተገለጸ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራው ልዑክ በጉጂ ዞን በሊበን ወረዳ ላይ ባደረገው ጉብኝት ሴት አርብቶ አደሮች ያሉበትን ደረጃ ተመልክቷል።

አርብቶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም ህይወታቸውን ለመምራት ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ይገደዱ እንደነበር ገልጸው፣ ይህ በህይወታቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት እንዳላስቻላቸው አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ ግን የክልሉ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በፈጠረላቸው ዕድል ከሚኖሩበት አካባቢ ሳይርቁ የሚያስፈልጋቸውን የመኖ እና የውሃ አቅርቦት በማዘጋጀት ወደ ከብት አደልቦ መሸጥ እንዲገቡ መደረጋቸው ተመላክቷል።

በቀበሌ ከሚደራጁ 40 ሰዎች 32ቱ ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉንና ሴት አርብቶአደሮችም በተለያዩ ዙሮች የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት ወደ ንግድ ስራ እንዲገቡ መደረጋቸውም ተገልጿል።

በዚህም በየግላቸው ከ10 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ትርፍ ለማግኘት መቻላቸውን ሴት አርብቶ አደሮቹ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ላይ ጥሩ የምጣኔ ሀብት ባለቤት መሆናቸውን ተከትሎ ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም ግን የገበያ ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ገበያ ልማት ኤጄንሲ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቡኔ ቱፋ፣ ችግሩ መኖሩ እንደሚታወቅ ገልጸው፣ ስራዎች እየተሰሩ እና ችግሮቹም እንደሚቀረፉ ጠቁመዋል።

ዜጎቹ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ለማስቻል በተግባር የተደገፉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ከሟሟላት ጀምሮ የገበያ ማዕከላትን መገንባት እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ዘጠኝ የእንስሳት የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)